"እዚህ የአበሻ ቀጠሮ የለም" ኢትዮጵያ ውስጥ ያደገችው ኖርዌያዊት ሀኔ
Description
ብዙዎች ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ „desyemil.amharic „ወይም „ሀኔ “ በሚል ስሟ ያውቋታል። ቲክቶክ ላይ በአጭር ጊዜ ከ 96 ሺ በላይ ተከታዮችን ማፍራት ችላለች።
ሀኔ 37 ዓመቷ ነው። የዘር ሀረጓ ኖርዌይ ቢሆንም በውስጧ ኢትዮጵያዊነት እንዳለ በምትሰራቸው ቪዲዮዎች ትመሰክራለች። ከኢትዮጵያ ጋር ያስተሳሰራት አጋጣሚ የጀመረው ገና በልጅነቷ ነው።
"የአባቴ ወላጆች ለተለያዩ ስራዎች ከ40 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖረዋል። በዚህ ምክንያት አባቴ ያደገው እዛው ነው። ከእናቴ ጋር ከተጋቡ በኋላ ደግሞ አብረው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለ10 ዓመት በዲላ ፣ሜጋ፣አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ኖረዋል። እኔም ያደኩት እዛ ነው። ወደ ኖርዌይ ስንመለስ የ10 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ አማርኛ እረሳሁ።" ስትል ታብራራለች።
ሀኔ አማርኛዋን ለማሻሻል ቆርጣ የተነሳች ይመስላል። በምትሰራቸው ቪዲዮዎች ላይ በተቻላት አቅም በአማርኛ ትናገራለች፤ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሳይቀር በአማርኛ እየፃፈች ታጠናለች። በድምሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ያህል እንደኖረች የምትናገረው ሀኔ ዛሬ ላይ አማርኛ ስታወራ አንዳንድ ሰዎች AI ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ነሽ ይሏታል።
"አማርኛ ስለምናገር፣ አማርኛ ስለምችል ፤ ባህሉንም ጭምር ። አንቺ AI ነሽ ይላሉ። አያምኑኝም" ትላለች። ያኔም ሀኔ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰነች፤ ሙዚቃ ለማዘጋጀት!
AI ነሽ ይሉኛል
«ሙዚቃውን በAI ነው የሰራሁት ለቀልድ ነው። እኔ መዝፈን ስለማልችል ግጥሙን ፃፍኩ እና የቀረውን በAI ነው የሰራሁት። የኢትዮጵያ ባህላዊ ዜማ እና የሴት ድምፅ ብዬ » ስትል ሙዚቃውን እንዴት እንዳዘጋጀች ስትናገር።
"እንደዚህ መዝፈን ብችል ዝነኛ በሆንኩ ነበር" የምትለው ሀኔ ለሌሎች ካጋራቻቸው ሙዚቃዎች በስተቀር ምንም አይነት AI እንዳልተጠቀመችም ትናገራለች።
ሀኔ አማርኛዋን ከማዳበር በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ መካከል የባህል ትስስር መፍጠር ትፈልጋለች። ቢያንስ በምትሰራው ቪዲዮዎች ሀኔ «ቡናድ» የሚባለውን የኖርዌይ ባህላዊ ልብስ ሌሎች ሰዎች ከሌሎች ባህላዊ አልባሳት ጋር አዋህደው የለበሱትን ስታይ እሷም « ኢትዮጵያዊ ጎኔን ማሳየት የምችልበትን ቡናድ» ልስፋ ብላ ተነሳሳች።
ከአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ ከገዛችው ጥበብ ጋር አቀናብራ የሰፋችውን ልብስ ለማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቿ ስታሳይም አድናቆት ችረዋታል። ሀኔ በአጠቃላይ ከሰዎች የምታገኛቸው አስተያየቶች ፈገግ ያስብሏታል።
"በጣም ብዙ አለ። ከቀልድ አንስቶ ውሰጂኝ ፣ላግባሽ ፣ውለጅልኝ የመሳሰሉት አይጠፉም። አማርኛ በጣም ጎበዝ ነሽ ። AI ነሽ አለ። ግን ለኔ ትልቁ ነገር ውጭ ሀገር ያደጉ ዲያስፖራ ወጣቶች የሚልኩልኝ መልዕክት ነው። ብዙዎች አማርኛ መናገር በደንብ አይችሉም። እና የእኔን ይዘት አይተው ቋንቋውን ለመማር እንደተነሳሱ ሲነግሩኝ። ደስ ይላል "
በአሁኑ ሰዓት ኖርዌይ የምትኖረው እና ፀሀይ እና ሙቀት እንደናፈቃት የምትናገረው ሀኔ በሙያዋ መምህርት ናት። "ለስደተኞች የኖርዌይን ቋንቋ እና ባህል አስተምራለሁ" ትላለች። መምህርትነቷ አልፎ አልፎም የምትሰራቸው ቪዲዮዎች ላይ ይንፀባረቃል።
ሀኔ ተሞክሮዋን በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ለማጋራት ምን አነሳሳት?
"ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ አስባለሁ። ቤተሰብ እዛ አለኝ። ኢትዮጵያ ያሉ ጓደኞች አሉኝ ።አሁን ደግሞ ሶሻል ሚዲያ ቀላል ስለሆነ ቋንቋውን ከመልመድ እና ከእኔ የሚማሩት ነገር ካለ ብዬ ነው።"
ሀኔ እግረ መንገዷንም የኢትዮጵያ ምግቦችን ማብሰል እየተለማመደች ነው። ቪዲዮ ቀርፃ የለጠፈችውን አዋዜ ጥብስ ብዙዎች የወደዱላት ሲሆን አንዳንዶች በሰጧት አስተያየት መሠረት እርሾ ሰርታ ሰሞኑን እንጀራ ለመጋገር ሊጥ ያቦካችበትን ቪዲዮ ለጥፋለች። ሀኔ ስለሚከብዳትም ነገር ትጠይቃለች። ኢትዮጵያውያን ስለ ኖርዌይ ቢያውቁ የምትለውም ስለ ቀጠሮ አያያዝ እና ሰዓት ማክበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነው።
"እዚህ አራት ሰዓት ከተባለ አራት ሰዓት ነው።የአበሻ ቀጠሮ የሚባል ነገር የለም"
ትክክለኛውን ከኢትዮጵያ የመጣ እና የጤፍ እንጀራ ለመግዛት እስከ 40 ደቂቃ በመኪና ነድታ የምትጓዘው ሀኔ ስለምትወዳቸውም የኢትዮጵያ ምግቦችም ነግራናለች። "ሽሮ፣ ክትፎ፣ ጭቅና ጥብስ፣ጨጨብሳ ፣ ቋንጣ ፍርፍር፣ ዶሮ ወጥ። ከዱለት እና ጥሬ ስጋ ውጪ ሁሉንም እወዳለሁ። ….የኢትዮጵያ ቡናን በተለይ የጀበና ቡና በጣም ነው የምወደው።"
ሀኔ ለአድናቂዎቿ እና ወጣቶች ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት?
„በማንነታችሁ እና በባህላችሁ መኩራት አለባችሁ“ የሚል ነው። እሷም ያደገችባቸውን ሁለት ባህሎች በኩራት እያቀረበች ትገኛለች። ሀኔ ያቦካችው ሊጥ በርግጥ እንጀራ ሆኖ እንደው ለማወቅ ከፈለጋችሁ „desyemil.amharic ብላችሁ ኢንስታግራም ወይም ቲክቶክ ላይ ብትፈልጓት ሰሞኑን አዲስ ቪዲዮ መለጠፏ አይቀርም።























